Sitota

ስጦታ

ከ አዲስ 2010 የተጻፈ

በቀደም እለት ካንዷ ጕደኛዬ ጋር ስናወራ እናም ካንዱ ወደ አንዱ ወሬ ስንዘል ድንገት ለስምንት አመት ልጇ አባቱ አይፎን መግዛቱን አወጋችኝ። እኔም በነገሩ በመደነቅ ለስምንት አመት ልጅ አይፎን አይበዛም ወይ? ብላት በርግጥ ውድ ነው ቢሆንም ልጄ ከሶስተኛ ክፍል ጥሩ ውጤት በማምጣቱ (ሰርፕራይዝ አደረግነው) ወይም ማስደሰት ፈልገን ነው አለችን!!
የስመንት አመት ልጅ አይፎን ተገዝቶለት ምን ያህል ደስተኛ ይሆናል?
ለስምንት አመት ልጅ አይፎን ምን ያደርግለታል?

ለስምንት አመት ልጅ ምን አይነት ስጦታ ይመጥነዋል? ስል በልቤ አሰብኩ ።
እስኪ እናንተም አስቡት? ከእኔ ጋር ልትስማሙም ወይም ልትቃረኑ ትችላላችሁ ። ለነገሩ እኔ የሷን ጫማ ተጫምቼ አላየሁት ይሆናል? ብቻ ፍርዱን ለናንተ ልተወው ።
እስኪ ራሳችንን እንጠይቅ? ስንቶቻችን ነን ለማን ፣ በምን ምክንያት ፣ ለምን? የሚለውን ጥያቄ አመዛዝነን ስጦታ የምንገዛው በርግጥ ስለወደድነው ብቻ ስጦታዎችን እንገዛልን ….. ይህስ ትክክል ይሆን ?እስኪ ተወያዩበት ?

አገር ቤት እያለሁ ማለትም ልጅ ፣ወጣት እና ጎልማሳ ሆኜ በትምህርቴ ጥሩ ውጤት ባመጣ ማለትም ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ ብይዝ ወላጆቼ ከሴትዬዋ ጋር ሳወዳድር ምን አይነት ስጦታ ያውም ከተሰጠኝ ነው!! ለምሳሌ አይፎን (ያን ጊዜ አይፎን የለም እንጂ)፣ ኮንጎ ጫማ ፣ ደብተርመያዣ የሸራ ወይም የፕላስቲክ ቦርሳ ወይስ አረንቻታ፣ ከረሜላ እኔ እንጃ ብቻ ሁሉንም ቢያደርጉልኝ እፈነጥዝ ነበር። አይፎን ቢገዙልኝ ግን ምን እንደሚሰማኝ አላውቅም!!

የስጦታ ትንሽ የለውም ከረሜላና አረንቻታ ትልቅ ሞራል ነው የሚሰጠው እናም አረንቻታ ሿሿ የሚለውን የነጻነትን ዘፈን እየዘፈንን ደስታችንን እንገልጽ ነበር። አሁንስ እኛ አብሶ ከሃገር ውጭ ያለነው ለስምንት አመት ልጅ ምን አይነት ስጦታ ይሆን የምንገዛው? አይፎን ወይስ አረንቻታና ከረሜላ? ይህን እናንተ ወላጆች አስቡት!! እኔ በወላጅና በልጆች መሃል መግባት አልፈልግም ሆሆ….
ብቻ በስምንት አመት እና ባስራስምንት አመት ልጆች መካከል ያለውን ትልቅ ልዩነት የሁሉም ግንዛቤ ነው ።

ስጦታ በባለትዳሮችና በፍቅረኛሞች መካካከል! እንዴት ፣ለምን፣ ምንስ አስመልክቶ? የሚለውን ጥያቄ በሁላችንም ዘንድ የሚጭር ይመስለኛል! ለምሳሌ ድንገት ሳያስበው ወይም ሳታስበው ከንፈሮቻቸውን በመሳም የፍቅር ስጦታ የልባችንን ፍቅር በስጦታ መልክ ማቅረብ ፤ በመልካም ቃላት በመነጋገር በጎበጎውን በማድነቅ ወዘተ…(በነገራችን ላይ የፈረንጆችን የፍቅር አገላለጽ ባህል ብዙም አላውቅም ፊልምና ሲኒማ በማየት ካዳበርኩት እውቀት ውጪ) ይህ ግን ለኛ ላበሾች የሚከብድ ይመስለኛል አብሶ ካደግን ውጪ ለተሰደድነው። የሆነው ሆኖ የስጦታ ትንሽ የለውም ያውም ከፍቅረኛ፣ከባል እና ከሚስት የሚበረከተለት ስጦታ(በተለያዩ ጊዜ ሾልከው ከሚወጡ አሜቶች እንደምንሰማው ከሆነ ውሽሞች ጥሩ የሚባል ስጦታ የመለዋወጥ ባህል ያላቸው ይመስለኛል ) አብሶ ወንዶቻችን እንዲረዱልን የምፈልገው እኛ ሴቶች ከባሎቻችን ወይም ከፍቅረኞቻችን ”ውሽሞቻችንን እንተውና” ምንም አይነት ቢሆን ስጦታ እንጠብቃለን ፍቅር የመጀመሪያውና ትልቁ ስጦታ ሲሆን ፤ ነገሩ ደረቅ በደረቅ እንዳይሆን የዚህ ጹሁፍ አቅረቢ አንዳንዴ አቅምን የመዘነ ስጦታ ያስፈልጋል ብላ ታምናለች ።ለምሳሌ የፍቅረኛሞች ቀን ሲከበር በየሱቆች በር ላይ ብዙ ማስታወቂያዎች ይታያሉ ታዲያስ ትንሽ ስጦታ ከጥሩ ቁረስ ጋር ከልብ በመነጨ አፍቅሮት ብናበረክት ፍቅርንም ሆነ ትዳርን ያድሳል የሚል አመለካከት አለኝ እናንተስ?
ከላይ እንደጠቀስኩት የስጦታ ትንሽ የለውም እላለሁ ነገር ግን አቅምን ያላገናዘበ ስጦታ ግን ትዳርንም ሆነ ፍቅርን ሊያጨልም ይችላል። ለምሳሌ ተበድሮ ለሚስቱ ያልማዝ ቀለበት የሚገዛ አባወራ ያለ ባይመስለኝም ፍቅረኛ ወይም እጮኛ ሊኖር ይችል ይሆናል። ይህ ሰው ሴትዬይቱን ለማስደሰት ያበረከተው ስጦታ ከልቡም ቢሆን እንኩአን ብድሩን በሚከፍልበት ወቅት ግን ሴቱቱን ማማረሩ አይቀርም ። እሷም ብትሆን ከፍቅር ይልቅ ያልማዝ ቀለበት ብትመርጥ ትርጉሙ አይገባኝም ፣ ለምን ቢባል ፍቅር ከልብ በመነጨ ቅንነት እነጂ በሃብት ብዛት አይገነባም ጌጥም የልብ ደስታ ከሌለ እንደ ተራ ድንጋይ ነው እላለሁ እናንተስ?

ለባሏስ መኪና በብድር የምትገዛ እማወራ አጋጥማችሁ አታውቅም ለምሳሌ እሷ መኪና መንዳት ባትችል ባሏን እንደግል ሹፌሯ ቆጥራ አድርሰኝ መልሰኝ ብትል በገዛ ዳቦዬ ልብልቡን አጣኩት እያለች ብትፎክር እዚያ ቤት ውስጥ የሚነሳውን ጦርነት አስቡት?ቀድሞውንስ ቢሆን መኪናው ያስፈልጋቸዋል እና እሷስ ብትሆን ባሏን እንደግል ሹፌር ማየቷ ተገቢ ነው? ወዘተ የመሳሰሉትን ጥያቄዎች ማስነሳቱ አይቀርም ።የዚህ ጹሁፍ አቅራቢ ይህ ሁሉ የስጦታና የማህበራዊ ኑሮ ውጥንቅቶች በኛ ማህበረሰብ ዘንድ ሊኖሩ ላይኖሩም ይችላሉ ብላ ታምናለች። ይህን ጹሁፍ ለመጻፍ ግን ያነሳሳት ካንድ እውነተኛ ታሪክ በመነሳት ሲሆን የኛስ ማህበረሰብ ለምን በነገሩ ዙሪያ አይወያይመ በሚል መንፈስ ብቻ ነው። በነገራችን ላይ ይን ጹሁፍ የጻፍኩት የዛሬ ሶስት አመት አካባቢ ሲሆን አሁን ባለንበት
ወቅት እና ሁኔታ ጋር አንድ አሳብ ላካትት እወዳለሁ። ነገሩ አንድ የግል ድርጅት የሰራተኞቹን የገና ስጦታ ሰብስቦ ለ ዩኒሴፍ በማበርከት 50ሺ ያህል የሚሆኑ ከትባቶችን ሊገዛ ችሎዋል የድርጅቱም ሰራተኞች በተደረገላቸው የገና ስጦታ ደስተኛ ሲሆኑ ሳይ እኛስ አገራችን ላይ ላሉ በቅርብም ሆነ የቆዩ ድርጅቶችን በገና ወቅት በምንሰጣጣው ስጦታ ለዚያ ብናውለው ብዬ አንዳንድ ወገኖች ያቀረቡትን አሳብ የበዚህ ጹሁፍ መዝጊያ ላደርገው ወደድኩ ።
መልካም ገና እና አዲስ አመት ለሁላችን ይሁንልለን